በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሀገራዊ የሎጅስቲክስ ሥራ እንዳይስተጓጎል በቅንጅት ለመስራት ስምምነት ላይ ተደረሰ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሀገራዊ የሎጅስቲክስ ሥራ እንዳይስተጓጎል በቅንጅት ለመስራት ከጅቡቲ መንግስት ጋር ከስምምነት ላይ ተደረሰ።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አወል ወግሪስ የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል የሎጅስቲክስ ሥርዓቱ ሳይተጓጎል መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከጅቡቲ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያ የገቢና የወጪ ንግድ በዋናነት ከጅቡቲ ወደብ የሚከናወን በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በጋራ በማድረግ በሁለቱም ሀገራት ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለመስራት ተስማምተዋል።
በሌላ በኩል መጨናነቅን ለማስቀረት በቀጣይ የወደብ አማራጭን ለማስፋትና የሎጅስቲክስ ወጪና ጊዜን ለመቆጠብ ታስቦ ከዚህ በፊት የተገነባውን የታጁራ ወደብ መጠቀም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ከሁለቱም ሀገራት የተውጣጣ ግብረ ሃይል አቋቁመዋል።
በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ በትኩረት በሚሰሩ ተግባራት ላይ የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ የታጁራ ወደብን በአማራጭነት መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ እና የወደቡን አገልግሎት ማስጀመር ላይ አስፈላጊ የሆኑ የወደብ አቅርቦት ለማሟላትና የጉሙሩክ አሰራር እንዲዘረጋ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ለማስጀመር የጋራ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ከትራንፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።