Fana: At a Speed of Life!

ዘንድሮ 25 ሚሊየን ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የበጀት ዓመት 25 ሚሊየን ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎች መታወቂያውን ለማግኘት የሚያስችላቸውን ምዝገባ ማከናወናቸው የተገለጸ ሲሆን÷ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 90 ሚሊየን ዜጎችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መታቃዱ ተገልጿል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያው የቀበሌ መታወቂያን ለመተካት ሳይሆን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሰጪዎች የግለሰቦችን ማንነት እንዲለዩ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራሔል አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት÷ በቀጣይ ሁኔታዎችን በማየት የዲጂታል መታወቂያና የቀበሌ መታወቂያ በተመጋጋቢነት ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ዜጎች ጊዜና ቦታ ሳይወስናቸው በኤሌክትሮኒክስ አማራጭ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ በ2015 ዓ.ም የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.