አስተዳደሩ በመዲናዋ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የውሀ ፓምፖችና ትራክተሮችን አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከ200 በላይ የውሀ ፓምፖችና 5 ትራክተሮች አበረከተ።
የውሀ ፓምፖቹና ትራክተሮቹን ያበረከቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና የአዲስ አበባ የብልፅግና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ካበረከተው የትራክተር ስጦታ በተጨማሪ የተለያዩ ባለሀብቶች የትራክትር ስጦታ አበርክተዋል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዳሉት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን ስንል ለሁሉም የተመቸች ከተማ እናደርጋታለን ማለታችን ነው፤ ይህ እቅድም አርሶ አደሮቻችን ያካተተ እንጂ የገፋ አይሆንም ብለዋል።
የግብርና ቁሳቁስ ስጦታው በአንድ በኩል በከተማዋ ሊፈጠር የሚችል የምርት እጥረትን ለመከላከልና የአርሶ አደሮችን የማምረት አቅም ለመጨመር ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሌላ በኩል አስተዳደሩ የጀመረውን የከተማ ግብርና መርሀ ግብር ለማበረታታት የታሰበ መሆኑን አውስተዋል።
አርሶ አደሮቹን መደገፍ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት እንዲሁም የምርት ፍላጎቱ እያደገ ላለው የከተማዋ ነዋሪ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።