ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ብሔራዊ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ በምስል የተደገፈ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን በኮቪድ19 ወረርሽኝ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ፣ በበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ የአደጋ አዝማሚያ እና በመጭው ወራት የአየር ፀባይ ትንበያ ዙሪያ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት፥ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር ተገቢ ነው።
የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመግታት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ የወሰዳቸው ትርጉም አዘል እርምጃዎች የሚያበረታቱ ቢሆንም፥ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰው ልጆችን በህይወት ጠብቆ የማሻገር ቁልፍ ተልዕኮ ያነገበ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ደመቀ፥ የወረርሽኙን አሳሳቢነት የሚመጥን ማህበረሰብ አቀፍ የባህሪ ለውጥ ማረጋገጥ እና የመከላከል ዝግጅቱን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የበርሃ አንበጣ ወረርሽኝ የአደጋ አዝማሚያ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እና የሚያስከትለውን ጉዳት ሊመክት የሚያስችል ቅንጅታዊ ርብርብ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
በመጭዎቹ ወራት የአየር ፀባይ ትንበያ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በሃገሪቱ ሊከሰት የሚችል የጎርፍ ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዙ የዝግጅት ስራዎች በፍጥነት ሊጠናቀቁ ይገባልም ብለዋል።
የብሄራዊ ኮሚቴውን ቁልፍ ተልዕኮ በጋራ ከማስፈፀም ባሻገር አባላት በዘርፉ ርብርብ እና በመዋቅር ቅንጅት በሚመጋገብ አግባብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።