ለሠራዊቱና ለሲቪል ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊቱ እና ለቋሚ ሲቪል ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት÷ የመከላከያ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ናቸው፡፡
በ26 ሺህ 673 ካሬ ሜትር ላይ ለ1 ሺህ አባወራ የሚተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የሚገነባው የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን መሆኑ ተገልጿል፡፡
ደረጃውን የጠበቀ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የዲዛይን ስራው መጠናቀቁን እና ግንባታውም በያዝነው ዓመት እንደሚጀመር የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብርጋዲየር ጀኔራል ደረጄ መገርሳ ተናግረዋል፡፡
የፋውንዴሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኮሎኔል ታደሠ ጌታቸው በበኩላቸው÷ የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎቹ ከ16 እስከ 18 እንደሚደርሱ ገልጸዋል፡፡
አንዱ ሕንጻም ከመሬት በላይ እስከ 12 ወለሎች (G+12) እንደሚደርስ መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም ግንባታው ባለ 1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤቶችን አጠቃሎ እንደሚይዝም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት አመራሮች በቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቁጥር 1 እና 2 ሳይቶች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጎብኝተዋል።