የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከተለያዩ የሀይማኖት መሪዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ ሠላምና ፀጥታ ዙሪያ ከተለያዩ የሀይማኖት መሪዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያዩ፡፡
በዉይይታቸዉም ክልሉ የተለያዩ የሀይማኖት ተከታዮች ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩበት የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ ክልል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሁሉም ሀይማኖቶች አስተምሮ ሠላም፣ ፍቅር፣ መቻቻልና አብሮነት ዋነኛ መርሆዎች ናቸው ሲሉም አክለዋል።
ይህንን ቅዱስ ተግባር የሀይማኖት መሪዎችና ታላላቅ አባቶች በየጊዜው ተከታዮቻቸውን ያለመታከት ያስተምራሉም ብለዋል።
በአማራ ክልል ዜጎች ያለገደብ በሠላም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ነግደው እንዲያተርፉ፣ ገበያው መረጋጋት እንዲችል፣ ህሙማን መድሃኒት እንዲያገኙና ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ እንዲችሉ ሠላም አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃቸውን አግኝተውና አምርተው እንዲያከፋፍሉ፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ያለምንም እንቅፋት አምርቶ ገበያ ባለበት ምርቱን እንዲሸጥና ያሰበውን እንዲያሳካ ሠላም ከሁሉም በላይ ትልቅ ዋጋ የሚከፈልበትና እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው÷ በክልሉ ሠላም እንዲሰፍን እና የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ የሠላምና የፀጥታ መስፈን ጠቀሜታ ወሳኝ በመሆኑ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግና ለተከታዮቻቸው በማስተማር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ለሰላም መስፈን ድርሻቸው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።