የቡና ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡና ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከ2 ሳምንት በኋላ የሚካሄደውን ስብሰባ በማስመልከት “ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ” ማህበር እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ስብሰባ “ዓለም አቀፍ ውሜን ኢን ኮፊ ኮንቬንሽ” የሚል መጠሪያ እንደተሰጠው በመግለጫው ተመላክቷል።
ከጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው ጉባዔ የዓለም አቀፍ ውሜን ኢን ኮፊ አሊያንስ /ህብረት/ አባል ሀገራት ይሳተፉበታል ተብሏል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሀመድ ሸምሱ ÷ በጉባዔው 300 የሚሆኑ የቡና ዘርፍ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ሁነቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ÷ የአሁኑ ስብሰባም በመስኩ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎለብት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውሜን ኢን ኮፊ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሳራ ይርጋ ÷ መድረኩ የውጭ ሀገር ገዥዎችን በቀጥታ ለመሳብ የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅም ምቹ አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል።
የስብሰባው ተሳተፊዎች ምርታቸውን የሚያቀርቡበት ኤክስፖ እንደተዘጋጀና በተመረጡ ቡና አምራች አካባቢዎች ጉብኝት እንደሚደረግም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡