ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር “ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ” ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የብሄራዊ ባንክ እና ሌሎች ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ፥ የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣንና ኢ – ተገማች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ የሳይበር ምህዳሩ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ እኩል የሚራመድና ለወቅቱ የሚመጥን እንዲሆን በማሰብ ረቂቅ ፖሊሲ መቀረጹን ገልጸዋል፡፡
ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ሳይበር ድንበር ተሻጋሪ ክስተትና ባህሪው ተለዋዋጭነት የሚታይበት መሆኑ፣ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሳይበር ደህንነት በይበልጥ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከአየር ንብረት ቀጥሎ ትልቁ የዓለም ስጋት የሳይበር ጥቃት እንደሆነ በመግለጽ የሳይበር ዲፕሎማሲን ለማሳደግ ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን ወቅቱን ያማከለ በማድረግ እንዲቀረጽ ትልቅ መነሻ ሆኗልም ነው ያሉት፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው÷የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም አካላት ሃላፊነት መሆኑን እና ይህንንም ለማረጋገጥ ዜጎች፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ጉዳይ እና ሃላፊነት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡