Fana: At a Speed of Life!

የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የጤና ፎረም እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች የጤና ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ፎረም “ጠንካራ አጋርነት፣ ትርጉም ያለው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ለተሻለ ጤና” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ/ር) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ በዚህ ወቅትም ሀገርን እያኮሩ የሚገኙ  መሆናቸው በመድረኩ  ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ÷ተቋማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የህብረትሰቡን ጤና ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አመታዊ ፎረሙ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶቸ እንዲሁም በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ አጋር አካላት በጋራ ሆነው የሚመክሩበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ፎረም የሚሳተፉ አካላት ያላቸውን ሀሳብና ልምድ የሚካፈሉበት ብቻ ሳይሆን የወጣቶችንና አፍላ ወጣቶችን ድምጽም የሚሰሙበትና የሚማሩበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ/ር) ÷ወጣትነት በትልቅ አቅምና ጉልበት የተሞላና ከፍተኛ የህይወት ለውጦች የሚስተዋሉበት የዕድሜ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ዴዔታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው÷ጤና ሚኒስቴር ለአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ወጣትነት አካላዊ አእምሯዊና ማህበራዊ ለውጦች የሚታዩበት ውድና ለየት ያለ ጊዜ መሆኑን በመግለጽ አንድ ሀገር የምትበለጽገው ወጣቶቿ ላይ በምትሰራው ስራ ነውም ብለዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.