የአድዓ- በቾ የከርሰ ምድር መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጥናት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የአድዓ- በቾ የከርሰ ምድር መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጥናት እና ዲዛይን መጠናቀቁን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ፕሮጀክቱ በደቡብ ኮሪያ መንግስት ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን÷ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በአድዓ፣ ሎሜ፣ ሊበን ጩቃላ፣ ኢሉ፣ በቾና ሰበታ ሐዋስ ወረዳዎች ላይ እንደሚገነባ ተገልጿል፡፡
5 ሺህ ሄክታር የሚሸፍነው ፕሮጀክቱ÷ ከከርሰ-ምድር በሚገኝ ውሃ በዘመናዊ መንገድ በመስኖ በማልማት 20 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
ግንባታው 42 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ ቀደም ሲል የተቆፈሩ ጉድጓዶችን የማጎልበት ሥራን ያካትታል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሮጀክቱን ወደ ግንባታ ለማስገባት የስራ ተቋራጮች ጨረታ ውድድር እየተካሄደ ሲሆን ግንባታው በስድስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ እንደሚጠናቀቅ ነው የተገለጸው፡፡