ስለጡት ካንሰር ምን ያህል ያውቃሉ ?
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር በጡት ውስጥ ያሉ ሴሎች ከተፈጥሯዊው ሁኔታ ወጣ ባለ መልኩ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን በሚራቡበት ጊዜ የሚፈጠር ህመም ነው፡፡
የአጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቬሮኒካ ጥላሁን በጡት ካንሰር ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም የጡት ካንሰር ሁለቱንም ጾታ እንደሚያጠቃ ገልጸው ፥ ነገር ግን አብዛኛው የጡት ካንሰር ሴቶች ላይ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ የተሰሩ ምርምርና ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የወንዶች ለጡት ካንሰር ተጋላጭነት ከ6 እሰከ 7 በመቶ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎችን በሁለት መልኩ ማየት እንደሚቻልና ይህም መቆጣጠር የማንችላቸውና የምንችላቸው በሚል እንደሆነ የህክምና ባለሙያዋ አንስተዋል፡፡
መቆጣጠር የማንችላቸው ሁኔታዎች ውስጥ÷ ሴት ሆኖ መፈጠር በራሱ ከወንድ አንጻር የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል ፤ ዕድሜ (የጡት ካንሰር በብዛት የሚከሰተው ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ላይ ነው) ፤የወር አበባ መምጣት ከሚገባው ጊዜ ቀድሞ ሲመጣ ፤ የወር አበባ ማየት ማቆም(ማረጥ) የሚዘገይ ከሆነ ፤ ለወሊድ መከላከያ የምንጠቀማቸው ኤስትሮጅን ሆርሞን የያዙ እንክብሎችን ለረጅም ጊዜ መጠቀም እና በቤተሰብ የሚመጣ ይጠቀሳል፡፡
መቆጣጠር የምንችላቸው ሆነው ነገር ግን አጋላጭ ምክንያቶች ደግሞ የአመጋገብ ዘይቤ ሲሆን ÷ ቅባትና ስጋ በብዛት መመገብ ፣ ፍራፍሬ እና አትክልት አለመጠቀም፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የጡት ካንሰር ምልክቶችም በጡት ላይ የሚከሰት እብጠት(ይህም ማለት ግን በጡት ላይ የሚከሰት እብጠት ሁሉ ካንሰር ነው ማለት አይደለም)፣ ጡት ጫፍ የሚወጣ ፈሳሽ(በተለይ ደም የቀላቀለ)፣ ከጊዜ በኋላ የመጣ የሁለቱ ጡቶች የመጠን መለያየት፣ የቆዳ መሸብሸብና ቀለም መቀየር፣ ከጊዜ በኋላ የመጣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ የብብት ውስጥ እብጠት ናቸው፡፡
የጡት ካንሰር ሕክምናም÷ የቀዶ ጥገና ሕክምና ፣ ኬሞቴራፒ(በደም ስር ወይም በእንክብል የሚሰጡ) ፣ የጨረር ሕክምና፣ የሆርሞን እንክብል ሕክምና እንዲሁም ‘’ታርጌትድ’’ ሕክምና(ለተወሰኑ ዓይነት የጡት ካንሰሮች የሚሰጥ)ናቸው ብለዋል፡፡