የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማት ለኮቪድ19 ክትባት መገኘት አስተዋፅዖ ያበረከቱ 2 ተመራማሪዎች አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮውን የሕክምና ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ለኮቪድ 19 ክትባት መገኘት አስተዋፅዖ ያበረከቱ ሁለት ተመራማሪዎች ማሸነፋቸው ተገለጸ።
ተመራማሪዎቹ ፕሮፌሰር ካታሊን ካሪኮ እና ፕሮፌሰር ድሩ ዌይስማን የዘንድሮውን የህክምና ዘርፍ የኖቤል ሽልማት እንደሚጋሩት ቢቢሲ አስነብቧል።
ፕሮፌሰር ካሪኮ እና ድሩ ዌይስማን የኖቤል ሽልማት ያሸነፉበትን ግኝት ለማጥናት ፍላጎት ያደረባቸው በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በሚገኘው የፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ሲሰሩ ነበር፡፡
አሁን ላይ ካታሊን ካሪኮ ሃንጋሪ በሚገኘው ዜጌድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፥ ድሩ ዌይስማን ደግሞ በአሜሪካ ፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በመሆን እየሰሩ ይገኛል።
ሁለቱ ተመራማሪዎች የደረሱበት ግኝት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን ወረርሽኙ ሲከሰት ግን ወደ ተግባር እንዲቀየር እና በንድፈ-ሐሳባቸው መሠረት ክትባት ተዘጋጅቶ ሚሊየኖች እንዲከተቡ መንገድ የከፈተ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
ንድፈ-ሐሳባቸውም ክትባቶች ቫይረስንና ባክቴሪያን እንዲለዩ በማድረግ የሰውን ልጅ የመከላከል አቅም ማሳደግ የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው።