Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ ክትትል ከሚደረግባቸው ምርቶች 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ክትትል ከሚደረግባቸው ምርቶች ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አማካሪ አቶ መስፍን አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሚኒስቴሩ ክትትል ከሚያደርግባቸው የቅባት እና ጥራጥሬ ምርቶች፣ የቁም እንስሳት፣ ጫት እንዲሁም የእንስሳት መኖ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ምርቶች በመጠን እና በጥራት ተመርተው እንዲላኩም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

በተለይ በቅባት እህሎች ላይ ያሉ ላኪዎችን ለማበረታታት በምርት ገበያ አካባቢ ያለውን ግብይት በኦንላይን እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በዚህም ላኪዎች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን ማመቻቸት እና የምርት ማስጠበቂያ ማሽኖችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት ፡፡

በተጨማሪ በጥራጥሬ ምርት ላይ የተሰማሩ ላኪ ድርጅቶች በተዘረጋው የግብይት መመሪያ መሰረት ምርቱን በክምችት ሳይዙ በወቅቱ ኮንትራት ገብተው ለዓለም ዓቀፍ ገበያ እንዲያቀርቡ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ይደረጋልም ብለዋል ፡፡

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በሰው ኃይልም ሆነ በላቦራቶሪ የኬሚካልና የአፍላቶክሲን መመርመሪያ ግብዓት እጥረት እንዳላባት ነው አማካሪው የገለጹት፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትም የጥራት መሰረተ ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ በዚህ ዓመት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ያሉት አማካሪው ፥ ይህም ችግሩን እንደሚፈታ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከመዳረሻ ሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጠናከር ጎን ለጎን በዓለም ዓቀፍ በሚካሄዱ ባዛሮች ላይ ምርቶችን የማስተዋወቅ ስራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኘውን ኮንትሮባንድ ለመከላከል ከሚኒስቴሩና ጉምሩክ ኮሚሽን ባሻገር ክልሎችም ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.