ኮርፖሬሽኑ በአዳማ ከተማ በ100 ሚሊየን ብር ለሚያስገነባው ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በአዳማ በ100 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚያስገነባው ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ፣ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ፣ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ተገኝተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አማካኝነት የሚያስገነባው ትምህርት ቤቱ በተለያዩ የግንባታ ምዕራፎች ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ የትምህርት ደረጃ የሚገነባ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የት/ቤቱ ግንባታ የስፖርት ሜዳ፣ የተማሪዎች ማረፊያና መዝናኛ እንዲሁም የአትክልትና አረንጓዴ ስፍራን የሚያካትት መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አክሊሉ ታደሰ ግንባታው በታቀደለት ጊዜ በጥራት እንዲከናወን እና የመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡