Fana: At a Speed of Life!

የእጅ ቦምቦችን ለሸኔ ለማቀበል ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች ዋስትና ላይ ዕግድ ተጣለ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)50 “ኤፍ 1” የእጅ ቦምቦችን ከ 8 የቦምብ ፊውዞች ጋር ለሸኔ ሽብር ቡድን ለማቀበል ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች ዋስትና ላይ ዕግድ ተጣለ።

እግዱን የጣለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሲሆን÷ተከሳሾቹም 1ኛ አማኑኤል ግርማ፣ 2ኛ አብዶ መላኩ እና 3ኛ ደጋጋ ፈቀደ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ በጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ሲያከናውንባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ፖሊስ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከሰበሰበ በኋላ የፍትኅ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ተረክቦ ክስ መስርቶባቸዋል።

በቀረበው ክስ ላይ ÷ተከሳሾቹ የኢፌዴሪ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ ቁጥር 10/2013 ሽበርተኛ ተብሎ የተሰየመውን ሸኔ የሽብር ቡድንን በቀጥታ እየረዱ መሆኑን እያወቁ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሶችን፣ ተተኳሽ ጥይት በማቅረብ እና ድጋፍ ማድረግ ላይ መሰማራታቸው ተመላክቷል፡፡

በተለይም 1ኛ ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀስ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል ከሆነው ነጋሳ ምሬሳ በትግል ስሙ አዱኛ ተስፋዬ ጋር በመገናኘት በነሃሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ አባል ነው የተባለው ግለሰብ ካሳሁን አማካኝነት ከአፋር ክልል አዋሽ ከተማ ቦምብ ይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ እና ተቀብሎ ”እኔ በምልከው ሌላ ሰው ትልክልኛለህ ” በማለት እንደተነገረው ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

1ኛ ተከሳሽም በጉዳዩ በመስማማት ጓደኛው ለሆነው ለ2ኛ ተከሳሽ ጉዳዩን በማሳወቅና ቦምቡን አብረው ሄደው ተቀብው ለማምጣት በመስማማት በቀጣዩ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ጋርመንት ወደሚባል ቦታ በመሄድ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ 50 ኤፍ ዋን (F1) የእጅ ቦምብ ከ8 የቦምብ ፊውዝ ጋር ማንነቱ ለጊዜው ካልተለየ ግልሰብ በመረከብ ወደ 2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት በመውሰድ ደብቀው ማስቀመጣቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

በነሃሤ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ባለቤቱና እናቱ ወደ ቤት እየመጡ መሆኑን እና ”ቦምቡን አውጥተን ሌላ ቦታ ማስወቀመጥ አለብን ” በማለት ለ1ኛ ተከሳሽ ከገለጸ በኋላ 1ኛ ተከሳሽም ሃሳቡን በመቀበል ጉዳዩን ጓደኛው ለሆነ ለ 3ኛ ተከሳሽ በማሳወቅ 3ቱም ተከሳሾች በሃሳቡ ተስማምተው ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ወደ 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመውሰድ አንድ ላይ በጋራ በመሆን ወደ 2ኛ ተከሳሽ ቤት መሄዳቸው በክሱ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ ቤት አውጥተው 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመደበቅና ለሸኔ ሽብር ብድን አባል ለሆነ ግለሰብ ለማቀበል በማሰብ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ በተደረገባቸው ክትትል በቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ 3ቱም ተከሳሾች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ሰፈራ ተብሎ የሚጣራ አካባቢ በሚገኝ የ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ከ50 ኤፍ ዋን (F1) የእጅ ቦምብ እና ከ 8 የቦምብ ፊውዝ ጋር እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ የሽብርተኛ ድርጅት የመርዳት ሙከራ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ያቀረበና ክሱም ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ የዋስትና መብት ይፈቀድልን ጥያቄ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሕገ-መንግስትና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ተረኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር።

ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል።

ክርክሩን የመረመረው ፍርድ ቤቱ የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና አያስከለክልም በማለት እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው ከስር እንዲፈቱ ፈቅዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ የፈቀደውን ዋስትና በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ተረኛ ችሎት ይግባኝ ጠይቋል።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የይግባኝ አቤቱታውን መርምሮ ያስቀርባል በማለት የስር ፍ/ቤት ለተከሳሾቹ የፈቀደውን ዋስትና ለጊዜው አግዷል።

ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ አቤቱታ ላይ መልስ ካላቸው ለመጠባበቅም ለጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.