አቶ አህመድ ሽዴ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያይተዋል።
በአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል።
በዛሬው ዕለትም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም የሚመክሩ ይሆናል።
የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የ650 ሚሊየን ዩሮ ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ መርሐ-ግብርም ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ አመራሮችና ቀጣናዊ ልዑካን ጋር ይወያያሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡