የአውሮፓ ኅብረት የ4 ነጥብ 3 ቢሊየን ፓውንድ ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን ለማድረግ ቃል ገባ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 22 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን ለገባችበት ጦርነት ድጋፍ ይሆን ዘንድ የ4 ነጥብ 3 ቢሊየን ፓውንድ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረት ቃል መግባቱ ተገለጸ፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ጆሴፕ ቦሬል ÷ አሁንም የ27ቱ ሀገራት ኅብረት “ጨካኝ እና ኢ-ሰብዓዊ” የሆነችውን ሩሲያ ለማሸነፍ ቁርጠኛ አቋም አለው ማለታቸውን ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።
ኅብረቱ ጉዳዩን አጥብቆ የያዘው እና መደበኛ ባልሆነ ስብሰባ የመከረው የአሜሪካ ምክር ቤት ለዩክሬን ማፅደቅ የነበረበትን ወታደራዊ ድጋፍ ችላ በማለቱ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ጆሴፕ ቦሬል ኅብረቱ በኪየቭ ያደረገውን የሰኞውን ያልተጠበቀ ስብሰባ ታሪካዊ ብለውታል፡፡
ነገር ግን ቀጣናው ያለበት ሁኔታ የኅብረቱ አባል ሀገራት ዩክሬንን ለመደገፍ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ዩክሬን ውጊያ ምቹ በነበረበት ወቅት አጋሮቿ ማየት የሚሹትን ድል አላሳየቻቸውምም ነው ያሉት፡፡
ወደፊትም የክረምቱ ወራት እየቀረበ እንደመምጣቱ መጠን ዩክሬን በእርዳታ ያገኘቻቸውን ታንኮች ለመጠቀም እንደሚቸግራት እና ጭቃ ስለሚይዛቸው ድል ሩቅ እንደሆነ ሀገራቱ ያስባሉ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በሌላ በኩል የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባሰፈሩት መልዕክት ÷ “ብቻ እናንተ አብራችሁን ሁኑ እንጂ በእርግጠኝነት ዩክሬን እና መላው ነፃ ዓለም ይህንን ጦርነት እናሸንፋለን” ብለዋል።
ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው ÷ ኅብረቱ አሁንም ከዩክሬን ጎን እንደሆነና በፈረንጆቹ 2024 የሚለቀቅ የ5 ቢሊየን ዩሮ (4 ነጥብ 3 ቢሊየን ፓውንድ) ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚያቀርግ ቃል መግባቱን ከዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡