Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል የመልስ መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ወደ እርማት አዳራሽ ሊገባ ነበር የተባለ ግለሰብ ተከሰሰ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 33 የመልስ መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ወደ ፈተና ማረሚያ አዳራሽ ሊገባ ነበር የተባለ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ሠራተኛ ተከሰሰ።

በተደረገ ክትትል በፍተሻ የመልስ መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ወደ እርማት አዳራሽ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው የተቋሙ ሠራተኛ ስልጣንን ያለአግባብ መገልግል የሙስና ወንጀል ተከሷል።

ተከሳሹ ይድነቃቸው ተኮላ ይኼይስ የሚባል ሲሆን÷ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ተረኛ ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት ነው ክስ ያቀረበበት።

በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው የስራ ማስታወቂያ ተመዝግቦ በፈተና አመቻችነትና ለእርማት ስራ በጊዜያዊነት መቀጠሩ በክሱ ተጠቅሷል።

በተለይም ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ውስጥ የተቀመጡና ለእርማት የተዘጋጁ የ18 ተማሪዎች የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መልስ መስጫ ወረቀቶችን ይዞ መውጣቱ በክሱ ሰፍሯል።

ከዚህም በኋላ በነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ 30 አካባቢ በፈተና ወቅት የተፈታኝ ተማሪዎች የመልስ መስጫ ወረቀቶች ያልሆኑና የፈተና መልስ ተቀልሞባቸው (ተሞልቶባቸው) የተዘጋጁ 33 የመልስ መስጫ ወረቀቶችን ደብቆ ወደ ፈተና ማረሚያ አዳራሽ ሊገባ ሲል በተደረገ ቁጥጥር በፍተሻ የተያዘ በመሆኑ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተገልጿል።

በተጨማሪም በተከሳሹ በመኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ 44 የ2015 ዓ.ም ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች የመልስ መስጫ ወረቀቶችና 10 ደግሞ ተመሳስለው የተዘጋጁ ሀሰተኛ የመልስ መስጫ ወረቀቶች የተገኙ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ ተከሳሹ ሥልጣንን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን ፥ በተረኛ ችሎት ክሱ እንዲደርሰው ከተደረገ በኋላ የዋስትና መብት ጥያቄ አቅርቧል።

በተከሳሹ የዋስትና ጥያቄ ላይ አቃቤ ህግ ዋስትና ሊፈቀድ እንደማይገባ ገልጾም ተከራክሯል።

ተረኛ ችሎቱ የግራ ቀኝ ክርክሩን መርምሮ በዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት በይደር የቀጠረ ሲሆን ፥ ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ላይ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ደግሞ ለጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.