ብሔራዊ የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመስከረም 28 እስከ 30 ይሠጣል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሠጠው ብሔራዊ የድህረ-ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመስከረም 28 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ተገለጸ።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ተወካይ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) በሁሉም የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን ለመማር የብሄራዊ ድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና መውሠድ በቅድመ ሁኔታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፥ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚሠጠው ብሔራዊ የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከመስከረም 21 ጀምሮ እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡
አያይዘውም፥ ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የልምምድ ፈተና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ ተፈታኞች በተመዘገቡበት ዩኒቨርሲቲ በመገኘት User name እና Password በመጠቀም የልምምድ ፈተና መውሰድ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፈተናው በተሣካ ሁኔታ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነው የገለጹት።