Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በ430 ሚሊየን ብር ወጪ የድጋፍ እህል ለመግዛት ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት 430 ሚሊየን ብር መድቦ በዝናብ እጥረት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የእርዳታ እህል ለመግዛት መወሰኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ።

ርዕሰ መሥተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች በሰጡት ማብራሪያ÷በክልሉ 8 ዞኖች እና 39 ቀበሌዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱ ነዋሪዎች ተቸግረዋል ብለዋል።

“ሕዝባችን ሲቸገር ቀድመን መድረስ አለብን” ያሉት አቶ አረጋ÷የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸውን አካባቢዎች ተዘዋውሮ በመመልከት የሕዝቡን ችግር ለይቶ ማወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ፈጣን ድጋፍ እንዲያገኙ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ነው ያስረዱት።

በእጃችን ላይ ያለውን ሃብት በመጠቀም የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ድጋፍ መላክ ተችሏልም ብለዋል።

“ችግሩ መጠነ ሰፊ ነው” ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ በክልሉ ያለው ለድጋፍ የሚውል ሃብት ውስን ቢሆንም ሌሎች አማራጮችን በሙሉ አሟጦ በመጠቀም ዜጎችን ከችግር ለማውጣት እንጥራለን ብለዋል።

የተወሰነው የ430 ሚሊየን ብር የድጋፍ እህል ግዥም ቢሆን በቂ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የችግሩን መጠን በመለየት ተጨማሪ ረጅ ድርጅቶችን የማፈላለግ እና የማስተባበር ሥራ ያከናውናል ነው ያሉት።

የተፈጠረው የዝናብ እጥረት አደጋ ከክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ ጫና ቢሆንም መንግሥት ለተቸገሩ ዜጎች ለመድረስ ሁሉንም አይነት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

የዝናብ እጥረት ያላጋጠማቸው እና ትርፍ አምራች የሆኑ አካባቢዎች ለተቸገሩ ወገኖች ፈጥነው በመድረስ ወገናዊ አለኝታነታቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ የተከሰተው የሰላም እጦት የድጋፍ እህል ለማጓጓዝ ፈተና እንደሆነ ማስረዳታቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡

“ለሁሉም ነገር መፍትሔ ለመስጠት መሠረቱ ሰላም ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ኀላፊነት የሚሰማው በሙሉ ለአካባቢው ሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።

በዝናብ እጥረት፣ በመፈናቀል እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.