የአዲስ አበባ ከተማ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ልምዱን ለክልሎች አጋራ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ያለውን የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ልምድ ልውውጥ መድረክ ለተለያዩ ክልሎች አጋርቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስላለፉት መልዕክት÷ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ ሚኒስትሮች፣ የኦሮሚያና የድሬዳዋ ከተማ አመራሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የመስኩ ባለሙያዎች በተገኙበት ልምዳችንን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አካፍለናል ብለዋል።
ባለፉት 2 ዓመታት ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥተን፣ የአስፈጻሚ ተቋማትን ቅንጅት ፈጥረን፣ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን በአሰራርና በአደረጃጀት ስራውን መርተናል ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡
በዚህም ወላጆችና አሳዳጊዎች በዕውቀት ሕጻናትን እንዲያሳድጉ 2 ሺህ 500 የቤት ለቤት ተንከባካቢዎችን አሰልጥነን አሰማርተናል ነው ያሉት፡፡
56 ጤና ጣቢያዎችንና 46 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን አሸጋግረን፣ 152 መዋዕለ ሕጻናትን እና 156 የመጫወቻ ስፍራዎችን በመገንባት÷ አዲስ አበባን የሕጻናት ማደጊያ ምርጥ አፍሪካዊ መዲና ለማድረግ በትጋት በመስራት ያካበትነውን ልምድ ነው ያጋራነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ለአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ልምዳቸውን ማካፈላቸው ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች÷ የትውልድ ግንባታ ስራችን ( የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም) የሀገር አቀፍ ትኩረት እንዲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መወሰኑን ጠቅሰዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!