ኢትዮጵያውያን ሳይዘናጉ በኮቪድ-19 ዙሪያ የወጡትን መመሪያዎች እንዲተገብሩ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሳሰቡ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 9 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉ ለአፍታም ሳይዘናጉ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የወጡትን መመሪያዎች እንዲተገብሩ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ባስተላፉት መልዕክት ቫይረሱን ለመከላከል ልንወስዳቸው የሚገቡ ርምጃዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጆችን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ በንጽሕና መያዝ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን በአግባቡ መጠቀም እና ለተወሰነ ጊዜ በቤት የሚቆይበትን ደንብ ተግባራዊ ማድረግን ይጨምራል ብለዋል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተጠቁት ሀገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ ያደጉ ሀገራት መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ሀገራትም በፍጥነት እርምጃ ባለመውሰዳቸው እና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው እንደተፀፀቱና ይህ ለኢትዮጵያም ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
አካላዊ ርቀት እና በሙሉ ወይም በከፊል ሕዝቡ በቤት እንዲቆይ የማድረግ እርምጃ የቫይረሱ ሥርጭት በአስከፊ ሁኔታ ሳይባባስ ተግባራዊ ከተደረገ፣ ሀገራት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እና በጤና አገልግሎት ሥርዓት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ይቻላሉ ብለዋል፡፡
ይህ ርምጃ ኢኮኖሚን እንደሚጎዳ ቢታወቅም፣ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሥርጭቱን ለመቀልበስ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ተጠቂ ከተገኘ ጀምሮ እስካሁን 317 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም፥ ቀስ በቀስ እያሻቀበ ይገኛል ብለዋል፡፡
የቫይረሱ በሀገራችን መገኘት በታወቀበት ሰሞን የሕዝቡ ምላሽ አዎንታዊና ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዳ ነበር ነውያሉት፡፡
መሠረት የሌላቸው መላምቶችም እየተሠነዘሩ በመምጣታቸው በርካታ ሰዎች የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ አካላዊ ርቀት መጠበቅንና እጆችን አዘውትሮ መታጠብን የመሰሉ ተግባራትን ቸል እንዲል ማድረጉን ገልጸዋል በመልዕክታቸው።
እንዲሁም ብዙ ዜጎቻቸው ሕይወት በቫይረሱ ከተቀጠፈባቸው፣ የጤና አገልግሎት ዘርፋቸው ከተናጋባቸው እና ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ከተቃወሰባቸው ሀገራት ስሕተት ለመማር ካልቻልን የምንከፍለው ዋጋ እጅግ አስከፊ ነው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።