የእስራዔል-ፍልስጤም ግጭት ቆሞ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲሳለጥ ብራዚል ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ የእስራዔል-ፍልስጤም ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሳለጥ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እንደሚሉት በእስራዔል እና በፍልስጤም መካከል ያለው ጦርነት ከቆመ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ማቆም ይቻላል፡፡
ሉላ ዳ ሲልቫ ሃማስ ያገታቸውን እንዲለቅ እስራዔልም የቦንብ ጥቃቷን እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ህጻናትን ከጥቃት ለመከላከልም አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሊደረስ ይገባልም ነው ያሉት።
የሚፈጠረው ከጦርነት ነፃ የመተላለፊያ መሥመርም ፍልስጤማውያን ሕጻናት እና እናቶች የጋዛን ሰርጥ አቋርጠው ወደ ግብፅ እንዲገቡ ያስችላል ሲሉ በማኅበራዊ ትሥሥር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
ብራዚል የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዚዳንት መሆኗ ይታወሳል፡፡
ከዚህ አንጻርም ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራታል መባሉን ሬውተርስ አስነብቧል፡፡