አቶ ኦርዲን በአረንጓዴ ዐሻራ የተገኘውን ውጤት በሌማት ትሩፋት ማስቀጠል ይገባል አሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ ዐሻራ የተገኘውን ውጤት በሌማት ትሩፋትም ማስቀጠል እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
አቶ ኦርዲን በክልሉ አቦከር ወረዳ ለሚገኙ 100 እማወራዎች የሌማት ትሩፋትን ለማስፋፋት የሚያግዙ ዶሮዎችን አበርክተዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ነው አቶ ኦርዲን በርክክቡ ወቅት የተናገሩት፡፡
በትጋት በመሥራት ፀጋዎቻችንና ሐብቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ዶሮዎቹ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው÷ የክልሉ መንግስትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው ÷ የሌማት ትሩፋት በክልሉ ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር ሚናው የላቀ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡