የናይጄሪያ አየር መንገድን ለማቋቋም ከሀገሪቱ መንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስታወቁ።
ይሁንና በቅርቡ በናይጄሪያ አዲስ መንግሥት መዋቀሩን ተከትሎ አየር መንገዱን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ማስፈለጉን አቶ መስፍን ጠቁመዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ናይጄሪያ አቡጃ በማቅናት ከሀገሪቱ መንግሥት ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱም የናይጄሪያ የመንግሥት አካላት ስለ ብሔራዊ አየር መንገዱ መቋቋም የፕሮጀክት ሂደት ለማወቅ ጥቂት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ‘እየጠበቅናቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ”ኤር ናይጄሪያ” የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን 49 በመቶ ድርሻ ይዞ ለማቋቋም በቂ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግሥትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጄሪያ ባለኃብቶች ጋር ሥምምነቶች መፈረማቸውም እንዲሁ።