Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረታችን ኢኮኖሚው ላይ መሆን ይገባዋል -ኢ/ር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 9፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ  የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረታችን ኢኮኖሚው ላይ መሆን ይገባዋል ሲሉ ገለጹ።

ኢንጂነር ታከለ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለብንን ፈተና በብቃት ለማለፍ  ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ኢኮኖሚዊ መዋቅር መገንባት የምንጀምርበት ወቅት አሁን ብለዋል።

ከንቲባው የኮሮና ቫይረስ የአለምን አጠቃላይ የኑሮ ቅርጽና ኢኮኖሚያዊ መዋቅርን በመረበሽ ዓለም ከረጅም ዘመን በኋላ የገጠማት ክስተት ሆኗል በዚህም ምክንያት ሀገራት ድንበራቸውን ዘግተዋል፣ዜጎች ወደ ፈለጉበት ቦታ የመንቀሳቀስ ሂደታቸውም ከመግታት ባለፈ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ሁነቶች ቁጥርም ከቫይረሱ መከሰት በኋላ ወደ ምንምነት ተጠግቷል ነው ያሉት፡፡

ቫይረሱ ከደቀነው የነዋሪዎች የመንቀሳቀስና በጋራ የመኖር ባህል ፈተና በከፋ መልኩ፣ የብዙሀን የአለም ዜጎች ሰርቶ መግባት ፈተና ውስጥ ገብቷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ስራቸውን አጥተው የመኖር ፈተና ውስጥ ወድቀዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያም የቫይረሱ መግባት ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ማህበራዊ ፈተናዎችን ደቅኗል በዚህም የዜጎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ የንግድም ይሁን የማምረቻ ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ ወድቋል፣ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳቢያ ስራቸውን ካጡ ዜጎች ባለፈ በተለይም በእለት በሚገኝ ገቢ ላይ ኑሮአቸውን የመሰረቱ ዜጎች ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ላይ ወድቀዋል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በወረርሽኙ ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመታደግ እንዲቻል ገንዘብና እርዳታዎችን ከማሰባሰብ ጀምሮ የምግብ ባንክን የመሳሰሉ ዜጎች ድጋፍ የሚያገኙባቸው መርሀግብሮች ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ  መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም እነዚህ የድጋፍ ስራዎች ችግሮችን ለአጭር ጊዜ ለማለፍ ቢያግዙም፤ ዘላቂ መፍትሄ መሆን ግን አይቻላቸውም ነው ያሉት አያይዘውም ዘላቂውና አዋጪው መፍትሄ የአኮኖሚውን ቅርጽ መጪውን ጊዜ ባገናዘበ መልኩ መዘርጋትና ማዋቀርና ስለሆነም ይህንን ለማሳካትትኩረት የምናደርግባቸው ዘርፎች መስተካከል ያሻቸዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እነርሱም መካከል ለዜጎች የስራ እድልን በሚፈጥሩ፣የገቢ ምንጭን የሚያጠናክሩ መሆን  እንዳለባቸው ጠቁመው÷ከነዚህ አንዱም የከተማ ግብርና ማስፋፋትና ከነዋሪዎች የእለት ተእለት ኖሮ ጋር ማስተሳሰር  መሆኑን አመላክተዋል።

አያይዘውም ይህ ዘርፍ ያለብዙ ወጪ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንድናገኝ ከመርዳቱም ባሻገር እስከዛሬ  ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በከተማ ውስጥ የሚገኙ መሬቶች ምርት የመስጠት አቅማቸው ከገጠሩ የተሻለ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የከተማ ግብርና በብቃት ከተሰራበት ኢኮኖሚውን በአስተማማኝ ደረጃ መደገፍ  ይችላል ስለሆነም ነዋሪዎቻችን የከተማ ግብርናን በመተግበር ራሳቸውን መመገብ ይችላሉ፣ይህ ደግሞ በስራ እጦት ለተቸገረው ነዋሪ አትራፊ መፍትሄና የምግብ አማራጭን  ከመፍጠሩም ባሻገር በአቅርቦትና ችግር ፣ በአማራጭ እጥረት፣ በዋጋ ንረት ለሚቸገረው ነዋሪም ፈተናዎችን ያቃልላል ነው ያሉት።

ከዚያም ባለፈ ለአምራቾቹ  አስተማማኝ የገቢ ምንጭ በመሆን በዘርፉ ወጣቶችን በሰፊው ማሳተፍ  ከማስቻሉ ባለፈ የከተማ ግብርና ለፈጠራ ስራዎች በር የሚከፍትና ለአካባቢያዊ ስነምህዳርም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆንም በተገቢው መጠን ላልሰራንበት የከተማ ግብርና ትኩረት በመስጠት የምግብ አቅርቦታችን ማሳደግ፣ የዋጋ ንረቶችን መቆጣጠርና ለነዋሪዎቻችን አዲስ የገቢ ምንጭ መፍጠርከእነዚህ ሁሉ ጋር በተቆራኘ መልኩ ደግሞ አረንጓዴ ልማትን ማፋጠን  እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ሌላው ኢኮኖሚያዊ መዋቅርን ለመገንባትና ፈተናዎችን ለማሸነፍ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ዘርፍ ሀገራዊ ሀብት የሆነው የሸክላ ስራና የሸማ ስራን ባቀፈ መልኩ የእደ ጥበብ ስራዎች ማሳደግና ማዘመን ላይ ነው ብለዋል፡፡

ከንቲባው አያይዘውም ዘርፉ ለብዙ ሰዎች የስራ እድልን ከመፍጠሩ ባሻገር ሀገራዊ በሆኑ ጥሬ እቃዎችና ረጅም የተጠቃሚነት ትስስር ባካተተ መልኩ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት መቻሉ ዘርፉ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ይጠቁመናል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች የተመቹ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን መገንባት መጀመራችን ለዘርፉ ለሰጠነው ትኩረት ማሳያ መሆን ይችላል።

አክለውም የዕደ ጥበብ ዘርፍን ዘመናዊ መልክ በማላበስ ለብዙ ዜጎቻችን የስራ አማራጭ እንዲሆንና በውጪ ሀገርም ገበያን በማፈላግ ሀገራዊ ጥቅሙን ማጉላት ላይ በስፋት መስራትም ይጠበቅብናልም ብለዋል።

ተስፋችንን መስራት ያለብን ራሳችን ነን! ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ፈተናዎችን በብቃት ማለፍ የሚያስችለን ኢኮኖሚዊ መዋቅር መገንባት የምንጀምርበት ወቅት አሁን   ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ  ገልጸዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.