Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ለውጪ ገበያ ከሚቀርቡ ማዕድናት 500 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊየን ማቲዎስ÷ እቅዱን ለማሳካት በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በተለይም የኩባንያዎችን የማልማት አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው÷ የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ጨምሮ በወጪ ንግዱ ላይ የማዕድናትን ስብጥር ለመጨመር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በሌላ በኩል በማዕድን ፍለጋና ማልማት ላይ የሚሰማሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቁጥራቸው እያደገ መምጣቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

በተለይም ለዓመታት በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ፍለጋቸውን ጨርሰው ወደ ማልማት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አላይድ ጎልድ ማይንኒን የተሰኘው የአውስትራሊያ የወርቅ አምራች ኩባንያ አካል የሆነው ኩምሩክ ማይኒንግ ኩባንያ እያከናወነ ያለው የወርቅ ማምረቻ ኩባንያንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኩባንያው የወርቅ ማዕድን ፍለጋውን ጨርሶ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ “በኢትዮጵያ ትልቁ የወርቅ ኩባንያ” ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን ማምረቻ እየገነባ እንደሚገኝም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

በኒኬል፣ ኮፐር፣ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሺየምና ሌሎች ማዕድናት የተሰማሩ ኩባንያዎች በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ፍለጋቸውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አብራርተዋል።

ከውጭ ኩባንያዎች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ባለኃብቶች በዘርፉ ለመሰማራት እያሳዩት ያለው ፍላጎት አበረታች እንደሆነ ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በማዕድን ዘርፉ ትልቅ ማነቆ የሆነውን ሕገ-ወጥ ምርትና ግብይት ለመቆጣጠር ከጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አስረድተዋል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.