የእርዳታ ሰራተኞች ወደ ጋዛ አቅርቦቶችን ለማድረስ ሰላማዊ መተላለፊያ እንዲከፈትላቸው ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእርዳታ ሰራተኞች ወደ ጋዛ የአደጋ ጊዜ የምግብ አቅርቦቶችን ለማድረስ ሰላማዊ መተላለፊያ እንዲከፈትላቸው ጠይቀዋል፡፡
በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 በእስራኤልና ሃማስ መካከል በተፈጠረው ጦርነት የተነሳ በጋዛ ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች በፍጥነት እያለቁ ነው ሲሉ የእርዳታ ሰራተኞች ተናግረዋል።
ድጋፉ በፍልስጤም ግዛት ወደ ግብፅ በሚያቋርጠው ብቸኛው ድንበር በራፋህ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገባ ሸምጋዮች ስምምነት እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ መሆኑም ተመላክቷል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድንበሩ እንደተከፈተ እርዳታ እንዲያደርሱ ለግብፅ ኤል-አሪሽ ከተማ እና በጋዛ ድንበር አቅራቢያ ለሚገኙ ከተሞች የምግብ አቅርቦቶችን መላኩ ተገልጿል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጋዛ ሰርጥ እና በዌስት ባንክ ለ522 ሺህ ፍልስጤማውያን ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።
ነገር ግን አሁን ያለው አስፈላጊ የምግብ ክምችት በቅርቡ ሊያልቅ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
ያለው ግብዓትም በመሰረተ ልማት መውደም እና በነዳጅ እጦት የተነሳ ወደ ሱቆች ወይም ወደ ህዝቡ መድረስ እየቻሉ እንዳልሆነም ተመላክቷል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የፍልስጤም ግዛቶች ዋና ዳይሬክተር ሳመር አብደልጃብር አብረዋቸው የሚሰሩ ዳቦ ቤቶችም ከቀን ወደ ቀን እየቀነሱ መምጣታቸውንና ያሉትም በውሃ እና በኤሌክትሪክ እጥረት የተነሳ በቂ ዳቦ ማምረት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ለሁለቱም ወገኖች ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ አምስት የጋዛ ጦርነቶች ሁሉ የከፋው ሆኗል ሲሉም ገልፀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!