Fana: At a Speed of Life!

እስራዔል ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ጋዛ እንዲተላለፉ ልትፈቅድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራዔል መንግስት ከግብፅ በኩል ወደ ጋዛ የሚደረጉ ሰብዓዊ እርዳታዎች ለሃማስ እስካልደረሱ ድረስ መተላለፍ የሚችሉ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ውሳኔው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በእስራዔል ቴል አቪቭ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የተደረሰ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት÷ እስራዔል በግብፅ በኩል በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን የሚደረጉ የውሃ፣ ምግብ እና ሰብዓዊ ርዳታዎች እንዲተላለፉ ትፈቅዳለች ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ለሃማስ ሊደርሱ የሚችሉ ማንኛውም አይነት እርዳታዎች እንዲተላለፉ አንፈቅድም ብሏል ፅህፈት ቤቱ፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትናንትናው እለት በቴል አቪቭ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ ከመጪው አርብ ጀምሮ ከግብፅ በራፋህ ድንበር በኩል ሰብዓዊ ርዳታዎች ወደ ጋዛ እንደሚደርሱ ገልጸዋል፡፡

ተመድ ለተጎጂዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያደርሳል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ እርዳታው ለሃማስ የሚደርስ ከሆነ ግን ሊቋረጥ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ግብፅ የራፋህ ድንበር ለሰብዓዊ እርዳታ ማስተላለፊያ እንዲውል በዛሬው እለት በይፋ ክፍት እንደምታደርግ መግለጿን አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.