ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነቷ ከታሪክ አንፃር ዘመናትን ያስቆጠረ ነው – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነቷ ከታሪክ አንፃር ከታየ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሬ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ ሃገራት ጋር ጭምር ንግድ ትለዋወጥ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል፡፡
በጅቡቲ በሶማሌ ላንድና በሶማሊያ የነበረ የቅኝ ገዥዎች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ወደ መሆን ያመጣ እና ወደ ኪራይም ያስገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ተሞክሮን መቀመር እና የራስን ኃላፊነት ከመወጣት አንፃርም መሰራት ያለበት ነገር እንዳለ ያስረዳሉ፡፡
የሰላምና ደህንነት ተመራማሪው ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታሪክም ቢሆን የራሷን እና የሌሎችን ሰላምና ደህንነት የምትጠብቅ ሀገር ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ከታሪክ በመማር ለመጠቀም መሞከር ይቻላል ብለዋል፡፡
መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስም ግብረ ኃይል ፈጥሮ መስራት እና የዲፕሎማሲውንም መንገድ ማቅናት ያስፈልጋል ሲሉም ምሁራኑ አስገንዝበዋል፡፡
በሃይማኖት ወንድራድ