ስፓርት

አውስትራሊያዊቷ ዋናተኛ በጀርባ ዋና ስፖርት የዓለም ክብረወሰንን ሰበረች

By Alemayehu Geremew

October 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የዋና ስፖርት ውድድር አውስትራሊያዊቷ ዋናተኛ ኬይሊ ማክዊን የጀርባ ዋና የዓለም ክብረወሰንን ሰብራለች፡፡

ኬይሊ ማክዊን 50 ሜትሩን የዋና ርቀት ለማጠናቀቅ 26 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶባታል፡፡

በዚህም በቻይናዊዋ አትሌት ሊዩ ዥያንግ በ2018 ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ12 ማይክሮ ሰከንድ ማሻሻል ችላለች፡፡

በ100 ሜትር እና 200 ሜትር የጀርባ ዋና የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ኬይሊ ማክዊን÷ በዋና ስፖርት በሦስት ርቀቶች ክብረወሰን በመስበር የመጀመሪያዋ አትሌት ሆናለች፡፡

በቡዳፔስት የተጎናጸፈችውን ድል ተከትሎ በሰጠችው አስተያየትም÷ “በማሸነፌ ደስ ብሎኛል፤ ውጤቱ በቀጣይ ለሚካሄዱ ውድድሮች በራስ መተማመን ይፈጥርልኛል” ብላለች፡፡

በሌላ በኩል በወንዶች የ50 ሜትር የጀርባ ዋና ስፖርት ውድድር ቻይናዊው ቺን ሃያንግ በ26 ሰከንድ ከ8 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ማሸነፉን ሲ ኤን ኤን ስፖርት ዘግቧል፡፡