Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያ የሆነውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አካሂደዋል፡፡

የሶስትዮሽ ወታደራዊ ልምምዱ ከሰሜን ኮሪያ ሊቃጣ የሚችልን የኒውክሌር እና የሚሳኤል ጥቃት መመከት የሚያስችል አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በኮሪያ ልሳነ ምድር በተካሄደው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ኒውክሌር የመሸከም አቅም ያለው የአሜሪካ ስትራቴጂክ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን መሳተፉ ታውቋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሳሪያዎች በልምምዱ ጥቅም ላይ መዋላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ÷ በኮሪያ ልሳነ ምድር ቀጣና የተካሄደው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ግልጽ የጠብ አጫሪነት ድርጊት ነው ስትል ኮንናለች፡፡

አሜሪካ መሰል የጦር መሳሪያዎቸን ወደ ቀጣናው ማንቀሳቀሷም የኒውክሌር ጦርነት እንዲጀመር የምታደርገው ትንኮሳ ነው ብላለች ፡፡

በአንጸሩ አሜሪካ ወታደራዊ ልምምዱ ዋሺንግተን ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳየት ያለመ ነው ስትል በፒዮንግያንግ የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች፡፡

ከዚህ ባለፈም ልምምዱ በኢንዶ ፓሲፊክ ቀጣና ከሚገኙ አጋር ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ማንሳቷን አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.