ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ታምናለች- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ኢትዮጵያ ታምናለች ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትአስታወቀ።
የ3ኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሞላል እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅ ደንብ እና መመሪያን በሚመለከት የሚካሄደው የሦስትዮሽ ውይይት ዛሬ በካይሮ ተጀምሯል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ውይይቱን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም÷በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በሚደረግ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ኢትዮጵያ ታምናለች ብሏል፡፡
በዚህ መሰረትም በድርድሩ ሒደት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት እንዲመጣ ለማስቻል ኢትዮጵያ በቅን ልቦና ትካፈላለች ነው ያለው።
ይህ ውይይት ሶስቱ ሀገራት ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት አካል ሲሆን÷በዚህ ሒደት ሀገራቱ የዓባይን ወንዝ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም የማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው መግለጫው ጠቁሟል።
አገልግሎቱ እነዚህ ውይይቶች ሦስቱ ሀገራት የሁሉንም ፍላጎት የሚያስጠብቁ የመግባቢያ ሃሳቦችን በማፍለቅ በትብብር እንዲሰሩ እንደሚያስችሏቸው አብራርቷል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራቱ የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ጥቅምና ስጋቶች ተረድተው በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ከተደራደሩ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ታምናለች ሲልም አስገንዝቧል፡፡