ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ህዝቦቿን ለመጠበቅ ነው- ጀኔራል አበባው ታደሰ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ህዝቦቿን ለመጠበቅ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡
ጀኔራል አበባው 116ኛውን የሠራዊት ቀን አከባበር አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ከዚህ ቀደም በነበረው ስርዓት ሠራዊት እንደ አዲስ የተደራጀበት በሚል ምክንያት የሠራዊት ቀን ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በተደረገው ሪፎርም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስትር በሠየመችበት ቀን ላይ ቀኑን ለማክበር መቻሉንም አስረድተዋል።
በዚህ መሠረትም ሰራዊታችን ከዛ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ሁኔታ ሁሉ በፈተና እየተሻገረ የመጣ ሃይል ስለሆነ የሠራዊቱ ቀን በዛ ቀን ሊከበር እንደቻለ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሰራዊት የነበራት ጠላቶቿ በተነሱባት ጊዜ ሁሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን ተልዕኮውን፣ ሀገሩን እና ህዝቡን እየጠበቀ የመጣና ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ሰራዊት ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።
የበዓሉ ዋና አላማ ለዘመናት ሀገራቸውን ከጠላት ለመፋለም መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን የምናከብርበትና ቃላቸውን በመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ቃለ መሀላ የምንፈፅምበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ባሳለፍነው ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በማየት ለቀጣይ ግዳጆቻችን ዝግጁ የምንሆንበት፣ እንደ ተቋም የተሠጠንን ሀገርን እና ህዝብ የመጠበቅ ሃላፊነት አጠናክረን የምንቀጥልበት እንዲሁም በሀገራችን በምንም አይነት መልኩ ትንኮሳ ሊቃጡ የሚችሉ ሀይሎች ካሉ አይቻልም የምንልበት በዓል ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጦር የምታዘጋጀው በዋናነት ህዝቦቿን ለመጠበቅ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ÷ በዓሉ ህዝባችን ሀገራችንን በመጠበቁ በኩል ከጎናችን በመሆን ሚናውን እንዲጫወት መልዕክት የምናስተላልፍበት ዕለትም ነው ሲሉ አክለዋል።
በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች በተቋም ደረጃ እየተከበረ መሆኑን ገልጸው÷የፊታችን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከህዝቡ ጋር በጋራ በማክበር የበዓሉ ፍፃሜ እንደሚሆን ጠቁመዋል።