የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ በቀለ ሙለታ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 ( ኤፍ ቢ ሲ)የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ በቀለ ሙለታ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
አቶ በቀለ ሙለታ ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ሌሊት ላይ ህይወታቸው አልፏል።
አቶ በቀለ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ለበርካታ አመታት በሃላፊነት አገልግለዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ፥ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸውና ጓደኞቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
በ1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተወለዱት አቶ በቀለ ሙለታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በወሰን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ወስደዋል።
ከየካቲት ወር 1986 ዓ.ም እስከ ጥር 2000 ዓ.ም ድረስ በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት ይዘጋጁ በነበሩ የተለያዩ ህትመቶች ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል።
ከየካቲት 2000 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2001 ዓ.ም ድረስ በዋልታ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን የአማርኛ ዜና፣ አርቲክልና መጽሔት ዋና አዘጋጅነት፤ ከሚያዚያ 2001 እስከ ሰኔ 2002 ዓ.ም ድረስ የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ፤ ከሐምሌ 2002 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ዋና ክፍል ኃላፊ፤ ከየካቲት 2004 እስከ ሚያዚያ 2006 ዓ.ም ድረስ የጥናትና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበበሪያ መምሪያ ስራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል።
ከየካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /የዜናና ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር፤ ከታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መርተዋል።
ከነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተቋሙን መርተዋል።
ከዚያም ከታህሳስ 07 ቀን 2013 እስከ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።
አቶ በቀለ፣ ባለትዳርና የአንድ ወንድና ሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።