የሩዝ ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት እያስመዘገቡ ከሚገኙ የግብርና ኢኒሼቲቮች መካከል ቀዳሚ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩዝ ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት እያስመዘገቡ ከሚገኙ የግብርና ኢኒሼቲቮች መካከል ቀዳሚ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አመለከቱ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከቁጭት ዕቅድ በኋላ ከታወጁ የግብርና ኢኒሼቲቮች መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት እያስመዘገቡ ከሚገኙት ውስጥ የሩዝ ልማት ቀዳሚ ነው ብለዋል።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሩዝ ልማት የመሬት ሽፋን በ10 እጥፍ መጨመር መቻሉንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የመሬት ሽፋን ከመጨመር ባለፈ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎትና ለተለያዩ አግሮ-ኢኮሎጂ የሚስማሙ የዝርያ አይነቶች እጥረት እንዲሁም የሩዝ መፈልፈያ ማሽን አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ከወዲሁ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የለማውን የሩዝ ሰብል የምርት ብክነትን በሚቀነሰ መልኩ ለመሰብሰብ የሚመለከተው አካል ሁሉ ዝግጁ እንዲሆንም አሳስበዋል።