Fana: At a Speed of Life!

ለእስያ ፓሲፊክ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት አምባሳደሮች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ገለፃ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የእስያ ፓሲፊክ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት አምባሳደሮች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገለጻ አድርጓል።

ገለጻው በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በአንጂነር ጌዲዮን አስፋው አማካኝነት ተሰጥቷል።

የገለጻው ዋና ዓላማ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ አምባሳደሮቹ ወቅታዊ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን እና በአሁኑ ሰዓት ሀይል ለማመንጨት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ፣ ግድቡ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ አህጉር የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተም ገለጻ ተደርጓል።

በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በትብብር፣ በፍሃዊነት እና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ኢትዮጵያ እየገነባች መሆኑም በገለጻው ተነስቷል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ውይይቶችን ማድረጋቸውን እና የነበሩ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ ከዚህ ደረጃ መድረሳቸውን፥ በቀጣይ የሚኖሩ ልዩነቶችንም በተመሳሳይ በሶስቱ ሃገራት በሚደረጉ ውይይቶች ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗም ተገልጿል።

ከገላጻው በኋላ አምባሳደሮቹ በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች ዓለም አቀፍ መርህን በተከተለ መልኩ በውይይትና በድርድር እንደሚፈቱ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ነው

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.