በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ መሬት ምዝገባ ትኩረት እንደሚሰጠው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የከተማ መሬት ምዝገባ በትኩረት እንዲከናወን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) አሳሰቡ፡፡
በከተሞች የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት ከተሞች የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆኑ መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የከተማ ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር፣ ኢ/ር)÷ በክልሉ የከተሞች ዕድገትን ተከትሎ የሚሰጡ አገልግሎቶች ያሉባቸውን ችግሮች እየፈቱ መሄድ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የሚስተዋሉ ችግሮች ካልተፈቱ በከተሞች የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
በክልሉ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የከተማ መሬት ምዝገባ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል በበኩላቸው÷ በከተሞች እየተስተዋሉ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የተለየ ስልት በመንደፍ መስራት ይገባል ብለዋል።
ከተሞችን ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየትና መፍትሔ በማፈላለግ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው ያሉ የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡