ታዋቂው የሲቪል መብት ተሟጋቹ ጀሴ ጃክሰን የአሜሪካ ኮንግረስ የህዳሴ ግድብንና ግብጽን በተመለከተ ኢትዮጵያን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያሳልፍ ጠየቁ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብን እና ግብጽን በተመለከተ የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያሳልፍ ታዋቂው የሲቪል መብት ተሟጋቹ ጀሴ ጃክሰን ጠየቁ።
ጀሴ ጃክሰን በኮንግረሱ ለጥቁር ኮከስ ቡድን መሪ ግብፅ ሰሞኑን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ስላስገባቸው ሰነድ ደብዳቤ ጽፈዋል።
በደብዳቤያቸውም ኮንግረሱ ናይል እና ግብጽን በተመለከተ ኢትዮጵያን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል።
አያይዘውም ግብጽ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ከዚህ በፊት ያለ ኢትዮጵያ ይሁንታ የተደረሱ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ለመተግበር ትሞክራለችም ነው ያሉት።
ለአብነትም በፈረንጆቹ 1929 እና 1959 የተደረሱ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ጠቅሰው፥ ስምምነቶቹ ግብጽ እና ሱዳን ያለ ኢትዮጵያና ያለ ሌሎች የናይል ተፋሰስ ሃገራት ይሁንታ የተፈረሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም ግብጽ እና ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የአንበሳውን ድርሻ በብቸኝነት እንዲይዙ የሚያደርግና ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የተደረሱ መርሆዎችን የጣሰ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጀሴ በደብዳቤያቸው እንዳሰፈሩት ግብጽ ኢትዮጵያን ሳታማክርና ሳታወያይ ናይል ወንዝን ተጠቅማ የአስዋን ግድብ መገንባቷንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከናይል ወንዝ 85 በመቶውን ድርሻ ታዋጣለች ያሉት ጀሴ፥ ይሁን እንጅ የተፈጥሮ ጸጋዋ የሆነውን የአባይ ወንዝን እንዳትጠቀም ግብጽ የምትከተለው አካሄድ ከህግም ሆነ ከሞራል አኳያ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ በግብጽ ላይ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ፀጋዋን የመጠቀም መብቷን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ እንዲያሳልፉም ነው የጠየቁት።
ካይሮም አሁን ላይ አሜሪካ እና የዓለም ባንክን በመጠቀም በሌሎች የተፋሰሱ ሃገራት ላይ የቅኝ ግዛት ውል ለመጫን እየሞከረች መሆኑንም በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ አንጻርም የአሜሪካ መንግስትም ሆነ የዓለም ባንክ የአደራዳሪነት ሚና እንደሌላቸው በማንሳትም አሜሪካም ከቅኝ ግዛት ውል እቅድ ልትወጣ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።