28 ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ስድስት የአውሮፓ ህብረት ዓባል ሀገራትን ጨምሮ 28 ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
እንግሊዝ የሀገራት መሪዎችን እና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን በአንድ የሚያሰባስበውን የመጀመሪያውን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ያተኮረ ጉባኤ በለንደን ማካሄድ ጀምራለች፡፡
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ እየተፈጠረ ያለው ቴክኖሎጂ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን ያለአግባብ መጠቀምን እና ስጋቶችን ለመቀነስ ዓለም አቀፍ የተቀናጀ ጥረቶችን በመቅረጽ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
ጉባኤው “የእኛን ጊዜ የሚገልጽ ቴክኖሎጂ” በሚል በሰየሙት በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ተመርቷል፡፡
በ28 ሀገራት እና በአውሮፓ ህብረት የተዘጋጀው የስምምነት ሰነድ በማዕከላዊ እንግሊዝ ብሌችሌይ ፓርክ የተስተናገደው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የደህንነት ጉባኤ በተከፈተበት ቀን ነው።
የስምምነት ሰነዱ በአደጋዎች፣ በእድሎች እና ለአለም አቀፍ ትብብር በተለይም በላቀ ሳይንሳዊ ትብብር ላይ የጋራ ስምምነት እና ሀላፊነት ለመመስረት ቁልፍ የሆኑ የመሪዎች ጉባኤ አላማዎችን የሚያሟላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።