በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ሕዝቡን ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ዳርጓል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ላለፉት ወራት በገጠሙት የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት÷ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የክልሉን ሕዝብ ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ዳርጎታል።
ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ለዘመናት በአብሮነት የሠራ ሕዝብ ከጋጠመው የሰላም እጦት በፍጥነት መውጣት አይከብደውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሮቻችን በውይይት ፈትተን ወደ ክልሉ ልማት እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ፊታችንን ማዞር ይጠበቅብናል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዮህ አቡሀይ በበኩላቸው÷ በክልሉና በከተማዋ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ ልማታችን ወደኃላ የተጎተተ መሆኑን ተረድተን ለሰላም መጠበቅ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የከተማዋ ሕዝብ ሕግ አዋቂ ነው እና በሕግ አግባብ ችግሮቹ እንዲፈቱ ሊጠይቅ ይገባል ሲሉም አንስተዋል።
ውይይቱ ጎንደር ያሉባትን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት በሰከነ መንገድ በነፃ ሃሳብ መነጋገርን ታሳቢ ያደረገ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል ።
“ሰላም ለሁሉም በሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ በተጀመረው የምክክር መድረክ ላይ ከጎንደር እና አካባቢው የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡