Fana: At a Speed of Life!

የሳንባ ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንባ ካንሰር ማለት በሳንባ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት ከመደበኛ ዕድገታቸውና ቁጥራቸው ውጪ ጤናማ ባልሆነ መልኩ መባዛት ነው፡፡

የሳንባ ካንሰር ከሳንባ ተነስቶ ወደ አንጎልና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጭ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለመሆኑ የሳንባ ካንሰር ምልክቶች ምንድናቸው?

ከሳንባ ካንሰር ምልክቶች ውስጥ የትንፋሽ ማጠር፣ የማያቋርጥ ሳል፣ ደም የቀላቀለ አክታ፣ ተደጋጋሚ የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ በመተንፈስ ወቅት ድምጽ መኖር፣ ባልታወቀ ምክንያት ክብደት መቀነስ፣ የጉሮሮ መዘጋት እንዲሁም የጀርባ፣ የደረትና የትከሻ ህመም ይገኝበታል፡፡

የሳንባ ካንሰር ህክምና ዋና ዋና አጋላጭ መንስዔዎች:-

ማጨስ፣ የአየር ብክለት፣ የቤተሰብ ሁኔታ (የሳንባ ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ በዘር የመተላለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ)፤ ከዚህ በተጨማሪም የጨረር ህክምና (በተደጋጋሚ በደረት ላይ የሚደረግ የጨረር ምርመራ ) በመንስዔነት ይጠቀሳል፡፡

የሳንባ ካንሰር ምርመራና ህክምና:-

የሳንባ ካንሰር ምርመራ ከሳንባ ውስጥ ናሙና በመውሰድ የሚካሄድ ሲሆን÷ በሳንባ ውስጥ የሚኖር እብጠት ወይም የተለየ ለውጥ በምስል ማለትም (የደረት ራጅ ወይም ሲቲ ስካን) በመመልከት ምርመራ ማካሄድ ይቻላል፡፡

የሳንባ ካንሰር እንደ ካንሰር አይነቱ እንዲሁም እንደሚገኝበት የስርጭት ደረጃ በብዙ መንገዶች የሚታከም ሲሆን÷ ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ ጨረር ሕክምና እና ሌሎች ዘመናዊ ህክምናዎች ወይም በእነዚህ ሕክምናዎች ጥምረት መታከም ይችላል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.