Fana: At a Speed of Life!

ርዋንዳ ለሁሉም አፍሪካውያን ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ርዋንዳ ለሁሉም አፍሪካውያን ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ ይፋ አድርጋለች።
እንደ አውሮፓ የሼንገን ዞን የሰዎችን በነፃነት መንቀሳቀስ እና መገበያየት ለማሳደግ አህጉሪቱ የያዘችውን ዓላማ ተከትሎ ርዋንዳ አፍሪካውያን ያለ ቪዛ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ መፍቀዷን በትናንትናው ዕለት አስታውቃለች።
ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃዱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ እምቅ አቅም ያላትና የቱሪዝም መዳረሻ የሆነችው አፍሪካ 60 በመቶው ከአፍሪካ ውጭ ባሉ ጎብኚዎች ጥገኛ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል፡፡
ካጋሜ በ23ኛው የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ማንኛውም አፍሪካዊ በፈለገ ጊዜ ወደ ርዋንዳ በአውሮፕላን መግባት እንደሚችልና ምንም አይነት ክፍያ እንደማይከፍልም ገልፀዋል።
“የራሳችንን አህጉራዊ ገበያ መዘንጋት የለብንም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “በመጪዎቹ አስርት ዓመታት መካከለኛ አቅማችን በፍጥነት ማደጉን ከቀጠለ አፍሪካውያን የዓለም አቀፉ ቱሪዝም የወደፊት እጣ ፈንታ ይሆናሉ” ብለዋል፡፡
በዚህም ርዋንዳ ለአፍሪካውያን የጉዞ ገደቦችን በማንሳት አራተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ትሆናለች ማለታቸውን ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።
ጋምቢያ፣ ቤኒን እና ሲሼልስ ሌሎቹ ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ የሚሰጡ ሀገራት ናቸው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.