Fana: At a Speed of Life!

ስለ የደም ሥር መዘጋትና ጋንግሪን ምን ያህል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደም ሥሮች በተለያየ ምክንያት በአጣዳፊነት ወይም ቀስ በቀስ ሊዘጉ ይችላሉ።

በሰውነት ውስጥ የተጣራ ደም ከልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚያሰራጩ “ደም ቀጂ (አከፋፋይ)” ደም ሥሮች እና ጥቅም ላይ የዋለ ደምን ይጣራ ዘንድ ወደ ሳንባ እና ልብ የሚመልሱ “ደም መልስ” ደም ሥሮች ይገኛሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት÷ ዋና ዋና ደም አከፋፋይ የደም ሥሮች ሲዘጉ በደም ሥሩ አማካኝነት ምግብና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ያገኝ የነበረው የሰውነት ክፍል (ለምሳሌ፡- እጅ፣ እግር፣ አንጀት፣ ወ.ዘ.ተ) ሊሞት ይችላል፡፡ ይህም “ጋንግሪን” ሆነ ይባላል፡፡

በእርግጥ እንደተዘጋው የደም ሥር ዓይነት እና ቦታ ታካሚዎች በ“ስትሮክ”፣ ልብ ድካም፣ በአንጀት መዘጋት ወይም በሌሎች ምልክቶች ምክንያት ወደ ሕክምና ተቋም ሊሄዱ እንደሚችሉም ነው የሚገልጹት፡፡

ለመሆኑ የደም ሥሮች በምን ምክንያት ሊዘጉ ይችላሉ?

የደም ሥሮች በልዩ ልዩ ምክንያት በአጣዳፊነት ወይም ቀስ በቀስ ሊዘጉ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡

ከአጣዳፊ ምክንያቶች መካከልም÷ በድንገተኛ አደጋ (በመኪና፣ በጥይት፣ በጩቤ፣ በማሽን አደጋ ወ.ዘ.ተ)፣ በደም መርጋት፣ ከልብ በሚበተን የረጋ ደም የሚሉት እንደሚጠቀሱ ያብራራሉ፡፡

ይህንን በመሰለው ችግር ምክንያት የሚመጣ የደም ሥር መዘጋት በአብዛኛው ፋታ እንደማይሰጥም ነው የሚያስገነዝቡት፡፡

በመሆኑም በአስቸኳይ የደም ሥር ሕክምና (ቀዶ ሕክምና) ካልተደረገ በሰዓታት ውስጥ ደም ያጠረው የሰውነት አካል (ለምሳሌ፡- እጅ፣ እግር፣ አንጀት፣ ወ.ዘ.ተ) ወደ መሞት (ጋንግሪን) ሊያመራ እንደሚችል ይገልጻሉ።

ቀስ በቀስ የሚከሰት ማለት ደግሞ÷ የደም ሥር መጥበብ ችግር ቀደም ሲል የነበራቸው ሰዎች ሲሆኑ ከአጣዳፊው ክስተት በፊት ሌሎች ምልክቶች ይኖራቸዋል ማለት ነው እንደባለሙያዎች ገለጻ።

ለምሳሌ፡- በሚራመዱበት ጊዜ የእግር ሕመም ይሰማል (በአብዛኛው ባት እና ታፋ ላይ)፣ ቆዳ ይደርቃል፣ ጥፍሮች ይጠነክራሉ፣ ወ.ዘ.ተ ሲሉ ቀስ በቀስ የሚከሰት የደም ሥር መዘጋት ምልክቶቹን ይጠቅሳሉ፡፡

ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ አስከፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ያለምንም እንቅስቃሴ በተለይም በመኝታ ጊዜ የእግር መርገጫ ዱካ እና ጣቶችን ማቃጠል፣ መቁሰልና መሰል ችግሮች ይኖራሉ ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፡፡

አጣዳፊ የደም ስር መዘጋት ምልክቶች?

የእጅ፣ እግር ደም ሥሮች መዘጋት የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳይ እንደሚችል በባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም ቀጥለው የተጠቀሱት ይገኙበታል፡፡

• የጣቶች ሕመም (ለምሳሌ፡- ማቃጠል፣ መደንዘዝ፣ ውሃ መቋጠር)፣
• ጣቶችን ጨምሮ እግርን እና እጅን ማዘዝ (ማንቀሳቀስ) አለመቻል፣
• የእጅ እና እግር መጥቆር እና ፈሳሽ ማምጣት፣
• የእግር የደም ሥሮች ሆድ ውስጥ ካለው ትልቅ የደም ሥር ጀምሮ ድንገት ሲዘጉ የሁለቱም እግሮች አለመታዘዝ ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ሕክምናው ምንድነው?

የደም ሥር በአጣዳፊነት ተዘግቶ ባለበት ሁኔታ የሚባክን እያንዳንዱ ሰዓት የእጅና የእግርን የመትረፍ ዕድል እያመነመነው እንደሚሄድ ባለሙያዎች በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

አለፍ ሲልም በሕይወት ላይ ጭምር አደጋ ሊያመጣ እንደሚችልም ያመላክታሉ፡፡

በመሆኑም ታካሚዎች በጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም ከሄዱ÷ እንደበሽታው መንስኤ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ማዳንን ታሳቢ ያደረጉ ሕክምናዎች ሊሠጡ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡

በአጠቃላይ እንደ ሕመሙ ዓይነት የሚወሰን ሆኖ ከታች የተዘረዘሩት የሕክምና ዓይነቶች ይሰጣሉ፡፡

• መድኃኒት በመስጠት (ለምሳሌ፡- ደም ማቅጠኛዎችን ጨምሮ እንደ ስኳርና የደም ግፊት ላሉ ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች)፣
• ቀዶ ሕክምና፣
• የረጋ ደምን መጥረግ፣
• ከአጣዳፊው የደም ስር መዘጋት/ደም መርጋት በፊት የነበረ (የከረመ) ለአጭር ርቀት የተዘጋ/የጠበበ ደም ሥርን መጠገን/መለጠፍ፣
• ከአጣዳፊው የደም ሥር መዘጋት/ደም መርጋት በፊት የነበረ (የከረመ) ረጅም የሆነ የደም ሥር መጥበብ ወይም መዘጋት) በሚኖርበት ጊዜ አማራጭ የደም ሥር በመንቀል ተቀያሪ የደም ሥር ሊሠራ ይችላል፣
• በአደጋ ምክንያት የተከሰተ የደም ሥር ጉዳት ሲሆን ደግሞ እንደ ጉዳቱ መጠን ቀጥታ በመስፋት፣ በሌላ ደም ሥር መለወጥን ጨምሮ ሌሎች ቀዶ ሕክምናዎች መስጠት።

ባደጉ ሀገራት ቀዶ ሕክምና ሳያስፈልግ በቆዳ በኩል ወደ ተዘጋው የደም ሥር ቱቦዎችን በማስገባት ደም ሥር የመክፈት ሕክምና በስፋት እንደሚሰጥ የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያዎች÷ ከነዚህም መካከል የረጋ ደምን ማቅለጥ እና መጥረግን ጨምሮ ሌሎች መንገዶች ይገኙበታል ይላሉ።

ነገር ግን እነዚህ ሕክምናዎች ዋጋቸው እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ በኢትዮጵያ ለበርካታ ታካሚዎች እንደማይቀርቡም ነው የሚያስረዱት፡፡

ቆርጦ ማስወገድ

ሕሙማን እጃቸው/እግራችው ከሞተ በኋላ ወደ ሕክምና ተቋም ከሄዱ ወይን አካልን የማዳን ሕክምና በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ቢቀር የሰውነት አካልን (የእጅ፣ እግር፣ ጣቶች) በቀዶ ሕክምና ማስወገድ ሕይወት ለማዳን አስፈላጊ ይሆናል ይላሉ ባለሙያዎች።

አንዳንድ ጊዜ ምንም እንኳን ጣቶችን ወይም ከዛ በላይ አካልን ማስወገድ ግዴታ ቢሆንም የቀረውን እጅን/እግርን ለማዳን ተጨማሪ የደም ሥር ሕክምና ሊያስፈልግ እንደሚችልም ነው የሚገልጹት፡፡

በመሆኑም የደም ሥር ሐኪም በሚገኝበት ተቋም ሌሎች ባለሙያዎች እጅ እና እግር ከመቁረጥ ውሳኔ በፊት የደም ሥር ቀዶ ሐኪም እንዲያማክሩ ይበረታታል፡፡

በተለይም በሽታው እንዳለበት የተጠረጠረ ሰው ሲኖር ጊዜ ሳይባክን ሕሙማንን ሕክምናው ወደሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች በፍጥነት ማስተላለፍ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.