Fana: At a Speed of Life!

የ“ቶንሲል” ሕመም እንዴት ይከሰታል?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ“ቶንሲል” ሕመም “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” ወይም የላይኛው መተንፈሻ ክፍል ሕመም ነው፡፡

ምንነቱ?

“ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) የሚያመላክተው የላይኛው የመተንፈሻ ክፍልን እብጠት ሲሆን፥ ይህም መቅላት፣ እብጠት መኖር፣ ቁስለትና ሌሎች ምልክቶች ይገለጻል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

መንስዔው?
“ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) ከአካባቢያዊ መጋለጥ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የሚገልጹት ባለሙያዎች÷ ለምሣሌ የትምባሆ ጭስ፣ የዓየር ብክለት፣ አለርጂ፣ ከቆሻሻ ንጥረ-ነገሮች፣ ትኩስ ምግቦችና መጠጦች ጋር በተያያዘ ሊከሰት እንደሚችል ያብራራሉ፡፡

እንዲሁም ከተላላፊ ተዋኅስያን ውስጥ አደገኛ የ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) መንስዔ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

በተጨማሪም “ቫይረሶች” ለሕመሙ መከሰት በምክንያትነት እንደሚጠቀሱም ነው የሚገልጹት፡፡

መተላለፊያው?
የላይኛው የመተንፈሻ አካላት “ኢንፌክሽኖች” የሚተላለፉት በአፍ ወይም በመተንፈሻ አካላት ንክኪ መሆኑንም ነው የህክምና ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡

ሕመሙ በአብዛኛው የሚከሰተው በመኸር፣ በክረምት እና በፀደይ ወቅት ነው ይላሉ፡፡
በአብዘኛውም በትምሕርት ቤት ዕድሜ (በሕጻናት ማቆያ ጭምር) ላይ በሚገኙ ልጆች ውስጥ ከታማሚው (ከተበከለ የመተንፈሻ አካላት) ፈሳሽ ጋር በመነካካት እንደሚተላለፍም ይገልጻሉ፡፡

አስተላላፊ ተዋኅስያን?

“ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመምን) ከሚያስከትሉ “ቫይረሶች” መካከል÷ “ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራኢንፍሉዌንዛ፣ አድኖ ቫይረስ፣ ኮሮና ቫይረስ፣ ኢንቴርኖ ቫይረስ፣ ራይኖ ቫይረስ፣ ሳይቶሜጋሎ ቫይረስ፣ ኤፕስታይነ-ባር ቫይረስ እና ሜታፕኒሞ ቫይረስ እንደሚገኙበትም ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያም÷ ከሞኖኒክሎሊስ በስተቀር አብዛኛው የቫይረስ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) ቀላል ነው፡፡

የሕመሙ ምልክቶች?

በባክቴሪያ የሚከሰት የ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) ምልክቶች ከሚባሉት መካከል÷ በድንገት የጉሮሮ መቁሰል፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የሆድ ሕመም፣ የቶንሲል እብጠትና መግል መሳይ ነጭ ፈሳሽ መቋጠር ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም የቫይረስ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” (የጉሮሮ ሕመም) ዋናዋና ምልክቶች የሚባሉት÷ የዐይን መቅላትና መቆጣት፣ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ሳል፣ ተቅማጥ፣ የድምጽ መጎርነንና የዐፍ ቁስለት ናቸው፡፡

ሕክምናውስ?

ለአብዛኛው የቫይረስ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” ሕመም ልዩ ሕክምና እንደማይሠጥ የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያዎች÷ ነገር ግን ልዩ ያልሆነ ምልክታዊ ሕክምና አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ከሕክምናዎቹ መካከል አንዱ የሆነው በዐፍ የሚወሰድ የሕመም ማስታገሻ ትኩሳትንና የጉሮሮ መቁሰል ሕመምን ያስወግዳል፡፡

አብዛኛው የ “ቶንሲሎፋርንጃይትስ” ሕመም በጥቂት ቀናት ውስጥ በራሱ ጊዜ ቢድንም፥ ሕክምና ማድረግ ግን ሕመሙ ከ12 እስከ 24 ሠዓት ድረስ የመዳን ጊዜውን ያፋጥናል ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡

የሕመሙ ምልክት ከታየ እና የምርመራ ውጤት ላላቸው ሕጻናት የ “አንቲባዮቲክ” ሕክምና አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ ይህ መዘግየት እንደሌለበትም ነው የሚያስገነዝቡት፡፡

የ “አንቲባዮቲኮችን” የመጀመር አስፈላጊነት?
• ሕክምናው ለ10 ቀናት በተመረጠ አንቲባዮቲክ የሚሰጥ ነው

• በሕመሙ ምክንያት የሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮችን ይቀንሳል

• የኢንፌክሽን ጊዜን ይቀንሳል

• ለሌሎች ማስተላለፍን ይቀንሳል

በሌላ በኩል በአንድ ዓመት ውስጥ ከሰባት ጊዜ በላይ የ “ቶንሲልፋርጂቲስ” ኢንፌክሽኖች ከተከሰቱ እንዲሁም ባለፉት 2 ተከታታይ ዓመታት ውስጥ በእያንዳንዱ ከአምስት በላይ የ “ቶንሲልፋርጂቲስ” ኢንፌክሽኖች ከተከሰተ የቶንሲል ቀዶ ጥገና ሕክምና ሊሰጥ ይችላል ነው የሚሉት፡፡

ምንጭ፡- የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.