ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በኮንፈረንሱ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ሶካ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳሉት÷ ኮንፈረንሱ ዜጎች ስለሳይበር ደህንነት ያላቸውን ግንዛቤና ንቃተ ህሊና በማሳደግ በሳይበር ጥቃት ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም ብቁ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ የራሱ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡
የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ ሊፈጥር የሚችለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ባለድረሻ አካላትም በጉዳዩ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሳይበር ጥቃት ደህንነትን ለማረጋገጥም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ብቁ እና ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ እና አሰራር ማዘጋጀት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው÷ የሳይበር ጥቃት በሀገር ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡