Fana: At a Speed of Life!

ሳዑዲ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ከሚባሉ የንግድ አጋሮች ውስጥ አንዷ ናት – አምባሳደር ምስጋኑ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ከሚባሉ የንግድ አጋሮች ውስጥ አንዷ ናት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

የኢትዮ – ሳዑዲ ግንኙነት ታሪካዊ ነው ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ ፥ የእስልምና እምነት ተከታዮች በስደት ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ጊዜ እንዳስቆጠረ ጠቁመዋል፡፡

በዚያን ጊዜ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ኢትዮጵያ ጥበቃ እና ዋስትና መስጠቷን አንስተው ፥ ለእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጓን አውስተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፖለቲካዊ ግንኙነት ባሻገር በሃይማኖትና በባህል የተሳሰረ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገራቱ በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አመላክተው ፥ በብሄራዊ ጥቅሞቻቸው ዙሪያ በጋራ የሚሰሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 1948 ይፋዊ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከተቋቋመ ወዲህ በሪያድ ኤምባሲ በጅዳ ደግሞ ቆንስላ ተከፍቶ ጠንካራ ግንኙነት ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትር ዴዔታው ፥ በዚህም ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በጸጥታ እና ደህንነት ትብበር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሳዑዲ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ከሚባሉ የንግድ ሸሪኮች ውስጥ አንዷ እንደሆነች ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የቁም እንስሳት፣ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና ሌሎች ጥሬ እቃዎችን ወደ ሳዑዲ ገበያ እንደምትልክ ጠቁመው÷ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረብያ ነዳጅ እና በርካታ ሸቀጦችን እንደምታስገባ አንስተዋል፡፡

ይሄን ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ200 በላይ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው እንደሚሰሩ ገልጸው ፥ በርካቶቹ ወደ ስራ ገብተው ምርት ማምረት መጀመራቸውንና ለ25 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

ከብሔራዊ ጥቅም አኳያም በቀይ ባህር አካባቢ ካለን ፍላጎት አንጻር ከሳዑዲ ጋር በጋራ መስራት ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሳዑዲ የአጀንዳ 2030 የልማት ግብ እንዳላት የጠቀሱት አምባሳደሩ ፥ በበርካታ ዘርፎች ላይ ትብብርን ማስፋት ታሳቢ እንደሚደረግ ነው ያነሱት፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ በምግብ ሰብል ላይ በሰፊው ኢንቨስት ማድረግ ትፈልጋለች ፤ በአረንጓዴ ልማት ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፤ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችም እንዲሁ በትኩረት እየተሰራባቸው ነው፤ በዚህም አጋርን በማብዛት ሳዑዲ ቁልፍ ሀገር እንደሆነች ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ግንኙነት ምሰሶ ሆነው የሚጠቀሱት የሃይማኖት፣ የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንደሆነ ጠቁመው ፥ ከዚህ አኳያ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እንደሚኖሩ ገልጸው ፤ የዜጎቻችን ጥቅም ተጠብቆ ባሉ የስራ ዕድሎችም ሆነ እንቅስቃሴዎች መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮ እንዲሰራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ዜጎች በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.