Fana: At a Speed of Life!

የሳዑዲ 2030 የልማት ግብ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳዑዲ ዓረቢያ 2030 የልማት ግብ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ( ዶ/ር) ሪያድ በተካሄደው የሳዑዲ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ ሳዑዲ ዓረቢያ ከአፍሪካ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላትና ለአህጉሪቱ እድገትም አስተዋጽኦ ማበርከቷን አውስተዋል፡፡

ሳዑዲ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷በአፍሪካ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ያላትን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡

በተለይም በአህጉሪቱ በታዳሽ ሃይል፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በግብርና፣ ጤና እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ፈሰስ በማድረግ ለአፍሪካ ዕድገት የምታደርገውን ጥረት አወድሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት እና ከሳዑዲ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ 2030 የልማት ግብ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሚናው የጎላ ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡

የልማት ግቡ በአምስቱ ቁልፍ የልማት ምሰሶዎች ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውንም ሳዑዲ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ የሳዑዲ ባለሃብቶች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጋብዘዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያላትን የጋራ ተጠቃሚትን መሰረት ያደረገ ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.