Fana: At a Speed of Life!

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ወደሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ለመመለስ ፍላጎት አለኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ወደሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ለመመለስ ፍላጎት እንዳላት ገለፀች።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር ለመደራደር ፍላጎት አላት ብሏል።

ሀገሪቱ ይህን ያለቸው ትናንት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና በሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ መካከል በግድቡ ዙሪያ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ውይይት ግድቡን አስመልክቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያልተቋጩ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ እና የተዛባ ግንዛቤ የነበረባቸውን ጉዳዮች ለማጥራት የታለመ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

በውይይቱም የአካባቢ ጥበቃ፣ የግድቡ የደኅንነት ሁኔታ እና የመረጃ ልውውጥን ስለ ማመቻቸት፣ በሱዳን በኩል ለተነሡት ጉዳዮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በውይይቱ ላይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ የሥራ ክንውኑ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል።

አክለውም፣ የሕዳሴው ግድብ ለሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት ኢኮኖሚ መጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የቴክኒክ ውይይቱን በሁለቱ ሀገራት የውኃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ለመቀጠል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ግብፅ ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ወስዳ እንደነበር አይዘነጋም።

ሆኖም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግደብን ውሃ ለመሙላት የየትኛውንም ሀገር ፈቃድ እንደማያስፈልጋት እና ሙሌቱን እንደማታዘገይ ግልፅ አድርጋለች።

በዚህ ክረምትም ግድቡ ውሃ ለመያዝ በሚያስችለው ከፍታ ላይ መድረሱን እና ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለፁ አይዘነጋም።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.