በአብዛኞቹ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታው በመሻሻሉ የሕዝብ አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት እስካሁን ያከናውናቸውን ተግባራት ገምግሟል፡፡
በዚህ ወቅትም ሕዝቡ ለጸጥታ ሥራው ተባባሪ የሚሆን ከሆነና ሰላሙ ወደነበረበት ከተመለሰ አዋጁ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ የሚጠናቀቅበት እድል እንዳለ ተመላክቷል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የሠራው ሥራ ውጤት እንዳመጣ በም/ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አሥተባባሪና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታው በመሻሻሉ የሕዝብ አገልግሎት እንደተጀመረ ማስረዳታቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር አልተላቀቁም፤ሕዝቡን ያሳተፈ ሥራ በመሥራት ሰላሙን ወደነበረበት መመለስ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ለሰላም ቁርጠኛ በመሆን ሰላምን ማስፈን እና በአካባቢው የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚነሳበት እድል እንዲኖር ማድረግ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡